Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለውን ህግ ማስከበር በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ክልሉን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው

በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለው የህግ ማስከበር ተግባር በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ክልሉን ወደ ሰለማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የአስአኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ አስታወቀ፡፡

በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርአት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ እንዲተገብር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መጠየቁ ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲተገበር በሙሉ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን፤ አዋጁን የሚያስተባብር ጠቅላይ መምሪያ እዝ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

በዛሬው እለትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መመሪያ እዝ ችግሩን ለመፍታት ያዘጋጀውን እቅድ አፈጻጸም በሚመለከት ውይይት አድርጓል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መመሪያ እዝ ዋና ሰብሳቢ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በሰጡት መግለጫ፤ በክልሉ በተደራጁ ዘራፊ ቡድኖች የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አስተዳደራዊ ችግሮችን ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

ዘራፊ ቡድኖች የህዝብ አግልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ከማስተጓጎል ባሻገር በአንዳንድ አካባቢዎች ማረሚያ ቤቶችን ሰብረው ወንጀለኞችን እንዲያመልጡ እስከማድረግ የደረሰ ውንብድና መፈጸማቸውን ጠቁመዋል::

ይህም በተለይ የክልሉ አርሶ አደር የመኸር እርሻ ወቅትን ተረጋግቶ እንዳያከናወን ማድረጉን ጠቅሰው፤ ዜጎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ በክልሉ የተከሰተውን የጸጥታ መደፍረስ ለመቀልበስ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ዘራፊ ቡድኑ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን በመዝረፍና በማውደም ጭምር የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ በደል እየፈጸመ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

መንግስት የትኛውም ጥያቄ በሰላም መፈታት እንዳለበት በጽኑ ያምናል፤ ባለፉት ጊዜያትም ይህንን በተግባር አሳይቷል ብለዋል፡፡

በቀጣይ መንግስት ህግና ስርዓት የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጭምር ነው የተናገሩት።

በክልሉ እየተከናወነ ያለው የህግ ማስከበር ስራ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ክልሉን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

ህብረተሰቡ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እንዲቆም እና ሰራዊቱን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.