በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የ13 ቢሊየን ብር ድጋፍ ተደርጓል -ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባጋጠሙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት መንግስት የ13 ቢሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማርያም እንደገለጹት ÷ በ2015 ዓ.ም በተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች፣ በአደጋ ስጋት ቅነሳ፣ በዝግጁነትና ምላሽ፣ በመልሶ ማቋቋምና በሃብት ማሰባሰብ ስራዎች አመርቂ ተግባር ተከናውኗል።
ሰው ሰራሽና የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ከፍተኛ ርብርብ መደረጉን ያነሱት ኮሚሽነሩ÷ ቅድሚያና ትኩረት የሚሹ 11 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች በጥናት ተለይተው የተለያዩ ድጋፎች ተደርገዋል ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ የተከሰተው ድርቅ ወደ ረሃብ እንዳይቀየር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን አመላክተዋል።
ለዚህና ለሌሎች ችግሮች ምላሽ ለመስጠት መንግሥት በመደበው 13 ቢሊየን ብር የተለያዩ ድጋፎች በማድረግ ስኬታማ ስራ ማከናወን እንደተቻለ ማንሳታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ለደረሰ አደጋ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ታቅዶ በመንግስትና በአጋር አካላት 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ምግብ መሰራጨቱን ጠቅሰዋል።
ከ4 ሚሊየን ለሚበልጡ ዜጎች ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁስና አልባሳት እንዲሁም ለ131 ሺህ ወገኖች ለመኖሪያ ቤት ጥገና አገልግሎት የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንም ገልፀዋል።
በአይነቱ ልዩ የሆነ የኢትዮጵያ የእሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት ተቋም ማደራጀት የሚያስችል የህግ ማእቀፍ ተዘጋጅቶ ለፍትህ ሚኒስቴር መቅረቡንም ጠቅሰዋል፡፡