ለጽንፈኛ ቡድኑ በሚዲያና በሎጅስቲክስ ድጋፍ ያደረጉ 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ ለጽንፈኛ ቡድኑ በሚዲያ በሎጅስቲክስ ሽፋን የሰጡና ለከተማ ግዳጅ የተዘጋጁ 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ገልጿል።
በቁጥጥር ስር በዋሉት ተጣርጣሪዎች ላይም ምርመራ እየተጣራባቸው ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡
ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በሰጠው መግለጫ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ፤ ተጠርጣሪዎቹ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከጽንፈኛ ቡድኑ ጋር ኔትዎርክ በማደራጀትና ትግሉን በማቀጣጠል በከተሞች ሆነው የሚዲያ ሽፋን በተለያዩ መንገዶች በማሰራጨት፣ ሎጂስቲክና ፋይናነስ የማሰባሰብ ስራ ተልዕኮ ወስደው ሲሰሩ በቁጥጥር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ÷ ለልዩ ግዳጅ ወደ ከተማ የገቡ ከፍተኛ የአጥፊነት ሚና የተወጡ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑንም አመልክተዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የኦፕሬሽን መምሪያ ፣ የሚዲያ መምሪያና የሌሎች ጉዳዮች አስተዳደር የድጋፍ የፖለቲካ ጉዳዮችን ካደራጀ በኋላ ቴክኒካል ቡድኖችን በማደራጀት ስራዎችን በየቀኑ እየገመገመና ኮማንድፖስት አደራጅቶ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ከ23ቱ ተጠርጣሪዎች ውጭ እስካሁን ድረስ በኮማንድ ፖስቱ የተያዘ ተጠርጣሪ አለመኖሩንም አረጋግጠዋል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎችም÷ ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ፣ ዶክተር ካሳ ተሻገር ዓለሙ፣ ተመስገን አበበ መስፍን፣ ዮሐንስ ንጉሴ ሙጨ፣ በቃሉ አላምረው ሽቱ፣ መላክ አያናው ጥጋቤ፣ ስንታየሁ ቸኮል ደጀኔ፣ ሊቁ እናውጋው ይሁኔ፣ ተመስገን ድልነሳ አለኸኝ፣ ጋሻነህ ላቀ ዘገየ፣ ፈጠነ ወርቄ ባንቴ እና ጌራወርቅ ብዙነህ ሲሳይ ናቸው፡፡
በተጨማሪም አማረ መለስ አከለ፣ ስመኘው አለምነው ሞላ፣ አማኑኤል አዳሙ ተስፋዬ፣ አትርሳው አለም ዘገየ፣ ትንሳኤ ኤልያስ በቀለ፣ ሳሙኤል ለማ ኃ/ገብርኤል፣ አድማሱ ዓለሙ ታየ፣ እታለም ኃ/ማርያም፣ ዮናስ ተ/ማርያም አደሮ፣ አባይነህ ዘውዱ ደመቀ እና ሕይወት ውብሸት ታደሰ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ውድመት ያደረሱ አካላትን አድኖ የህግ ማስከበር፣ አጥፊዎችን ወደ ህግ የማቅረብ ስራ እና የምርመራና የማጣራት ስራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡
በአመለወርቅ ደምሰው