Fana: At a Speed of Life!

የመሰረተ ልማት ተቋማትን ደኅንነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተመላከተ

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2015 ኤፍ ቢ ሲ) ቁልፍ የመሰረተ ልማት ተቋማትን ደኅንነት ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጥናት ባካሄደባቸው ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳቸው ጉልህ በሆኑ የተመረጡ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች በሚስተዋሉ የደኅንነት ስጋቶች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል።

በውይይቱ ለተቋማቱ የሚደረግ የደኅንነት ጥበቃ ስራ ከሚደርሰው ሀገራዊ ጉዳት እና ካለባቸው ስጋት አንጻር የሚመጥን መሆን እንዳለበት ተመልክቷል።

በተለይ የተቋማቱ አካላዊ ጥበቃን በሰለጠነ የሰው ኃይል ማጠናከር እንዲሁም የአደጋ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም በጥናቱ ተጠቁሟል።

ቁልፍ መሰረተ ልማቶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚኖረውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ስራዎች ላይ በማሳተፍ በማህበረሰቡ ዘንድ የእኔነት ስሜት መፍጠር እንደሚገባም ተገልጿል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ ÷የጥናቱ ትኩረት የተቋማቱ የደኅንነት ስጋት መጠን የሚያደርሰውን ሀገራዊ ጉዳት ያገናዘበ መሆኑ አመላክተው የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የደኅንነት ስጋት በጥናቱ የተካተቱ ቁልፍ የመሰረተ ልማት ተቋማት ችግር ብቻ እዳልሆነ በመጠቆም፤ ወደፊት በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ቁልፍ የመሰረተ ልማቶች ላይ ተመሳሳይ ጥናት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የፌዴራል ፖሊሲ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ እንደገለጹት÷ የደኅንነት ስጋት የሚቀረፈው በፀጥታ አካላት ብቻ ሳይሆን የባለድርሻ አካላትን አሳትፎ በጋራ በመስራት መሆኑን አብራርተው የፀጥታ አካላት የቁልፍ የመሰረተ ልማቶችን ደኅንነት ለመጠበቅ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.