Fana: At a Speed of Life!

በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን በገላን ከተማ የበላይነህ ክንዴ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮምፕሌክስ የመኪና ማምረቻ እና መገጣጠሚያን ጎብኝተዋል፡፡

በዚህም በድርጅቱ የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

አቶ በርኦ ሀሰን በ10 ዓመት ውስጥ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ 148 ሺህ አውቶሞቢሎችን እና 48 ሺህ አውቶብሶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እቅዱን ከተያዘው ጊዜ ቀድሞ ማሳካት እንደሚቻል በርካታ ማሳያዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ያደረገው የቀረጥ ማበረታቻ፣ የባለሃብቱ ተነሳሽነት እና የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ዘርፉ በፍጥነት እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው አንስተዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ማዕከላትን ለማስፋፋት ከመንግስት ተቋማትና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር በመነጋገር ማዕከላቱ የሚገነቡበት ቦታ እንዲያመቻቹ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የበላይነህ ክንዴ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮምፕሌክስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማምረትና በመገጣጠም ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ እቅዱን ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.