በህገ ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ የተሳተፉ የንግድ ተቋማት ተገኙ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በህገ ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ የተሳተፉ የንግድ ተቋማት በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ገንዘቦች ይዘው በፖሊስ ተደርሶባቸዋል።
ተቋማቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ድርጅት ጋር በቅንጅት ባከናወነው ኦፕሬሽን ነው በቁጥጥር ስር የዋሉ፡፡
ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ ጥቆማ በቦሌ ክፍለ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ መጠጥ ቤቶች በተከናወኑ ኦፕሬሽን በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ገንዘቦች ተይዘዋል።
መጠጥ ቤቶችበህጋዊ የንግድ ሽፋን ስም በጥቁር ገበያ ( ህገ ወጥ) የገንዘብ ምንዛሬ ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደነበርም ተረጋግጧል፡፡
በአጠቃላይ በአስራ አንድ ቤቶች በተደረገው የጥናትና የኦፕሬሽን ስራዎች በአምስቱ ላይ የኢትዮጵያን ጨምሮ የ15 ሀገራት ገንዘቦች ከነ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ከተያዙት ገንዘቦችም ውስጥ 2 ሚሊዩን 916 ሺ 800 የኢትዮጵያ ብር፣ 54 ሺ181 የአሜሪካ ዶላር፣ 34 ሺ 50 ዩሮ፣ 305 የእንግሊዝ ፓውንድ፣ 7 ሺ 719 የሳውዲ ሪያል፣ 11 ሺህ 440 ድርሀም፣ 52 ሺ የሊባኖስ ፓውንድ፣ 80 ሺ640 የሱዳን ፓውንድ እንዲሁም የተለያዩ ስድስት ሀገራት የገንዘብ ኖቶች ተይዘዋል፡፡
በህጋዊ የንግድ ስራ ሽፋን ተሰማርተው መሰል የወንጀል ተግባራት ውስጥ የሚገቡ የንግድ ተቋማት ላይ በጥናት ላይ የተመሰረተ የወንጀል መከላከል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡