Fana: At a Speed of Life!

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ አካሄደ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ ዓመት ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባኤ አካሂዷል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በጉባዔው ለውይይት የሚሆን መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በዚህም ለሀገር ዘላቂ ሰላም እና ልማት መንግስት የተቀናጀ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመንግስት ሁሉን አቀፍ ጥረቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላት ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሰላም እና ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የምክር ቤት አባላት ከመቼውም ጊዜ በላይ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ነው አቶ ኢብራሂም የተናገሩት።

ምክር ቤቱ በአስቸኳይ ጉባዔው የተለያዩ ሹመቶችንም እንደሰጠ የድሬዳዋ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም መሰረት አቶ ሱልጣን አልይ የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ፣ ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ የአስተዳደሩ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ ወ/ሮ ሁክሚያ መሀመድ የሴቶችና ሕፃናት ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ፣ ጫልቱ ሁሴን የአስተዳደሩ ምክር ቤት የሴቶች ሕፃናት ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን ተሹመዋል።

ዕጩዎችን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት÷የተካሄደው የስልጣን ሽግሽግና አዲስ ሹመት የህዝብን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በፍጥነት ለመመለስ የሚያስችል ነው።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የተሰጣቸውን መሠረታዊ ተልዕኮና ኃላፊነት በአግባቡ ከመወጣት አንፃር ተገምግመው እስከ 14 የሚሆኑት ከስልጣን እንዲነሱ ተደርጓልም ብለዋል።

በአፈጻፀም ብቃታቸውና ባስመዘገቡት ውጤት ወደ ስልጣን እንዲመጡ የተደረጉ አዳዲስ ባለስልጠናት መኖራቸውን ጠቁመው÷ “ይህም የተሻለ ውጤታማ ሥራ ለመስራት ሲባል የተከናወነ ነው” ብለዋል።

ድሬዳዋን ወደ ተሻለ ከፍታና ዕድገት ለማድረስ የሚከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን እገዛም አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.