የአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ተመራቂዎች የሚያጋጥሙ ተለዋዋጭ ሥጋቶችን ለመመከት አቅም እንደሚሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ሥልጠና የወሰዱ ባለሙያዎችን አስመርቋል፡፡
በምርቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ÷ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በንቃት ሊቃኙ የሚገባቸው ወቅታዊና ተለዋዋጭ አደጋዎች አሉበት ብለዋል፡፡
እነዚህን አደጋዎች ቀድሞ መለየትና መከላከል መቻል ኢንዱስትሪው ሰላማዊና ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና ይጫወታልም ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኞችና መሠረተ-ልማቶች ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን አገልግሎቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አመርቂ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ተመራቂዎች የአየር መንገዱን ደኅንነት በማረጋገጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ፈጣንና ለደንበኞቹምቹ አገልግሎት መሥጠት የሚችል እንዲሆን ለማድረግ በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምቹና ደንበኞቹ እምነት የሚጥሉበት ሆኖ እንዲቀጥል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የጀመረውን ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
ሠልጣኞቹ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ለመለየትና ለመከላከል የሚያስችላቸውን መሠረታዊ ሥልጠና በፅንሰ-ሐሳብና በተግባር እንዲቀስሙ መደረጉም ተጠቁሟል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው÷ሠልጣኞቹ የአቪዬሽን ዘርፉን ከማናቸውም አይነት አደጋ ለመጠበቅ የሚያስችላቸውን ሥልጠና መውሰዳቸውን አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል የአሜሪካ ትራንስፖርት ደኅንነት ቢሮ ሃላፊ ዴቪድ ፔኮስኬ÷ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ዲጂታል ኤግዚቢሽንና በአገልግሎቱ ስር የሚገኘውን የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ የሥራ እንቅስቃሴ መጎብኘታቸው ተገልጿል፡፡