Fana: At a Speed of Life!

ቻይና የአፍሪካን ቀጣናዊ የምጣኔ ሐብት ውኅደት ለማሳለጥ ቁርጠኛ ነኝ አለች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ቻይና የአፍሪካን ቀጣናዊ የምጣኔ ሐብት ውኅደት ለማሳለጥ ቁርጠኛ መሆኗን አስታወቀች፡፡

የቻይና አቋም ይፋ የሆነው በትናንትናው ዕለት ከተካሄደው የቻይና-አፍሪካ የመሪዎች ውይይት በኋላ መሆኑን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡

ቻይና የአፍሪካን ወጪንግድ በማጠናከር እና በማስተሳሰር እንዲሁም የቀጣናውን ኢንቨስትመንት በማስተዋወቅ ረገድ የበኩሏን እንደምትወጣም መሪዎቹ ባወጡት የጋራ አቋም መግለጫ ተመላክቷል፡፡

የአፍሪካ መሪዎችም በአቋማቸው ቻይና ለጀመረችው የዓለምአቀፋዊ ዕድገት ፣ ደኅንነት እና ሥልጣኔ ኢኒሼቲቮች ዕውቅና ሰጥተው ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ኢኒሼቲቮቹ ብዝኀነትን ለማጠናከር ብሎም በቻይና – አፍሪካ የልማት ትብብር የዓለምን ሠላምና ልማት ለማረጋገጥ አጋዥ እንደሚሆንም መግለጫቸው አመላክቷል።

ሁለቱ ወገኖች ÷ የቻይና-አፍሪካ ውኅደት ከፍተኛ ጥራት ባለው የ”ቤልት ኤንድ ሮድ” ትሥሥር እውን እንደሚሆን በጋራ መግለጫቸው አረጋግጠዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረትን “አጀንዳ 2063” እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራትን ብሔራዊ የዕድገት ስትራቴጂዎች በማቀናጀት የቻይና-አፍሪካ ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ነው ያመላከቱት፡፡

የጋራ መግለጫው ÷ በአኅጉሪቱ የሚስተዋሉ የጸጥታና ደኅንነት ተግዳሮቶችንና ሥጋቶችን ለመቅረፍ ብሎም ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ የጋራ ማዕቀፍ እና ሥልት መንደፍ እንደሚገባም አስምሮበታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.