አሜሪካ ዩክሬንን ”የተሰጠሽን መሣሪያ ቆጥበሽ ተጠቀሚ” አለች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የአሜሪካ ወታደራዊ ዕቅድ አውጪዎች የዩክሬን አጋሮቻቸው እስከ አሁን የተሰጣቸውን ወታደራዊ ድጋፍ ቆጥበው እንዲጠቀሙ መምከራቸው ተገለጸ፡፡
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት አሜሪካ በተለያየ መልኩ ለዩክሬን ድጋፏን ስትሰጥ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም የአሜሪካ ወታደራዊ ዕቅድ አውጪዎች ዩክሬንን ከዚህ በኋላ የተሠጣትን የጦር መሣሪያ ቆጥባ እንድትጠቀም መክረዋል፡፡
አክለውም ፥ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት የሚሠጣቸው ሥልጠና ላይ እንዲቆዩ ማሳሰባቸውን አር ቲ ወል ስትሪት ጆርናልን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ምንም እንኳን ወታደራዊ ድጋፏን እሷና አጋሮቿን እያስተባበረች ለ3 ወራት ስታደርስ ብትቆይም ዩክሬን ወደ ሩሲያ ጥሳ ለመግባት በመዛሏ ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ለዩክሬን የደረሳት ድጋፍ ለጦርነቱ በቂ ነው ብላ ታምናለች፡፡
የባይደን አስተዳደር ለዩክሬን የመደበውን ገንዘብ በሙሉ ማውጣቱ የተነገረ ሲሆን ፥ ከዚህ በኋላም እስከዛሬ በምታደርገው ልክ ወታደራዊ ድጋፍ እንደማትሰጥም በዘገባው ተዳሷል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለአሜሪካ የአደጋ ጊዜ መውጫ 40 ቢሊየን ዶላር እንዲያጸድቅ እና ከዚህም ግማሽ ያክሉን ለዩክሬን እንዲመደብ የሀገሪቱን ኮንግረስ መገፋፋታቸውም ነው የተሰማው።
ለዚህም ምላሽ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ኬቨን ማካርቲ “ገንዘብ ዝም ተብሎ አይበተንም” ሲሉ ፕሬዚዳንቱ የሚሉትን የገንዘብ መጠን እንደማያጸድቁ ቀደም ሲል ገልጸዋል፡፡