ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ማህበረሰቡ የዓይን ብሌኑን በመለገስ ለወገኖቹ ብርሃን እንዲሆን ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ዜጎች ከህልፈት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን በመለገስ ለሌሎች ወገኖቹ ብርሃን እንዲሆን ጥሪ አቀረቡ፡፡
ፕሬዚዳንቷ የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ የተመሰረተበት 20ኛ ዓመት አከባበር ላይ እንደገለጹት÷ ማህበረሰቡ ስለ ዓይን ልገሳ ያለውን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ ማከናወን ይገባል፡፡
ከህልፈት በኃላ በሚደረገው ልገሳ ምንም የምናጣው ነገር አይኖርም ያሉት ፕሬዘዳንቷ÷ ብርሃንን የመሰለ ታላቅ ስጦታ ትኩረት ሊነፈገው አይገባም ብለዋል፡፡
ስለሆነም ዜጎች ከህልፈት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን በመለገስ ለሌሎች ወገኖቻቸው ብርሃን እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የበርካታ ሰዎችን ህይወት የለወጠ ተቋም ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡
እስካሁን የዓይን ባንኩ ባደረገው እንቅስቃሴ ከ3 ሺህ ለሚበልጡ ወገኖች ብርሃናቸውን መመለስ መቻሉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡