ሩሲያ በማሊ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲራዘም በፈረንሳይ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ተቃወመች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በማሊ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲራዘም ፈረንሳይ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ያቀረበችውን የውሳኔ ሃሳብ ሩሲያ ውድቅ አድርጋለች፡፡
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ማሊ ወታደራዊ ጁንታ በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ባቦከር ኬታ መፈንቅለ መንግስት በማካሄዱ በተመድ ማዕቀብ ተጥሎባት ቆይቷል፡፡
የማዕቀቡ የጊዜ ገደብ በትናንትናው እለት ማብቃቱን ተከትሎ ፈረንሳይ እና የተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች በማሊ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲራዘም ተመድን ቢጠቁም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላት ሩሲያ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ አድርጋለች፡፡
በተመድ የሩሲያ አምባሳደር ቫዚሊ ኔቤንዝያ÷ ሀገራቱ ያቀረቡት የውሳኔ ሃሳብ የሞስኮ እና ባማኮን ፍላጎት ያላገናዘበ ነው ብለዋል፡፡
ፈረንሳይ እና የተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች በማሊ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እስከ ፈረንጆቹ 2024 እንዲቆይ ያቀረቡት የውሳኔ ሃሳብ የ13 ሀገራትን ድምፅ ቢያገኝም በሩሲያ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ውድቅ ተደርጓል፡፡
ቻይና ባንፃሩ ውሳኔውን በተመለከት ድምፅ ተዓቅቦ ማድረጓን አርቲ ዘግቧል።