Fana: At a Speed of Life!

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መታወቂያን አስመስሎ በማዘጋጀት ሰዎችን እያስፈራራ ገንዘብ ሲቀበል ነበር በተባለ ተጠርጣሪ ላይ ክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ተቋም መታወቂያን አስመስሎ በማዘጋጀት ሰዎችን እያስፈራራ ገንዘብ ሲቀበል ነበር በተባለ ተጠርጣሪ ላይ ክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።

የክስ መመስረቻ ጊዜ ለዐቃቤ ሕግ የፈቀደው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሲሆን÷ተጠርጣሪው ነስሩ ሳሌ ጀማል ይባላል።

ግለሰቡ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሰራተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት ደህንነት ነኝ በማለት ግለሰቦችን በወንጀል እንደሚፈለጉ በመግለፅና መታወቂያውን በማሳየት ከግለሰቦች እስከ 200 ሺህ ብር ጀምሮ ሲቀበል እንደነበር ተመላክቷል፡፡

በዚህም ሀሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት የሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ሲከናወንበት መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ በዛሬው ቀጠሮ የምርመራ ስራ ማጠናቀቁንና መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን ለተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስታውቋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክተር ዐቃቤ ሕግ ችሎት ቀርቦ የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ መረከቡን ገልጿል።

መዝገቡን ተመልክቶም ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ተጠርጣሪው በበኩሉ ÷ ከዚህ በፊት ለፖሊስ ተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ መፈቀዱን ጠቅሶ በድጋሚ ለክስ መመስረቻ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ አይገባም በማለት የዋስትና መብቱ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ችሎቱ ዐቃቤ ሕግ መዝገቡን ተመልክቶ ክስ ለመመስረት ጊዜ እንደሚያስፈልገው በማመን የተጠርጣሪውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለዐቃቤ ሕግ የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።

ውጤቱን ለመጠባበቅም ለመስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.