ሜዲካል ጎዝ እና የወረቀት ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሜዲካል ጎዝ እና የወረቀት ምርቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢንድስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በአዳማ ከተማ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በኩሪፍቱ የወረቀት ማምረቻ ድርጅት ፣በአዳማ ፈትል ፋብሪካ እና ናዝሜድ ሜዲካል ቴክስታይል ጉብኝት ያደረጉት ሚኒስትሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሀገር ውስጥ ፍላጎታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምርቶችን በማምረት ላይ መሆናቸው ተመልክተናል ብልዋል፡፡
በተለይም በከፍተኛ ወጪ ወደ ሀገር የሚገቡትን የወረቀት ምርቶችና የሜዲካል ጎዝ በአጥጋቢ ሁኔታ እያመረቱ ይገኛሉ ያሉት አቶ መላኩ ምርቶቹን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካዎቹ በስራ ዕድል ፈጠራውም ዘርፍ ከ 1ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ስራ ፈጥረዋል ያሉት ሚኒስትሩ በግብዓት እጥረት ምክንያት ምርት እንዳይቀንሱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይም ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪው የሀገር በቀል ኢኮኖሚው ደጋፊና በተኪ እና ወጪ ምርት እንደ ሀገር እንደርስበታለን ብለን የወጠነውን ትልም እንዲሳካ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በ2015 በጀት አመት የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አመራሮችና ባለሙያዎች የእውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል።
በጎህ ንጉሱ