በሆንግ ኮንግ ከባድ አውሎ ነፋስ መካከል ማረፍ የቻለው ብቸኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787 -9 ብቸኛው በሆንግ ኮንግ ከባድ አውሎ ነፋስ መካከል ማረፍ የቻለ በመሆኑ ዓለም አቀፍ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምቹ ያልሆነ የአየር ሁኔታን በመቋቋም አውሮፕላኑን በሆንግ ኮንግ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሰላም እንዲያርፍ አድርጓል።
በወቅቱ የሆንግ ኮንግ የአየር ሁኔታ “ታይፎን ሳኦላ” በተሰኘ በሰዓት 210 ኪሎ ሜትር በሚጓዝ ከባድ አውሎ ነፋስ የተነሳ ለበረራ ምቹ እንዳልነበረ ተመላክቷል፡፡
በዚህም ሌሎች በርካታ አየር መንገዶች በሆንግ ኮንግ አደገኛ የአየር ሁኔታ በረራቸውን መሰረዛቸው ነው የተነገረው።
ከባድ ውሳኔ የወሰነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787-9 በረራ የዓለምን ትኩረት የሳበ እና በዓለም አቀፉ የበረራ መቆጣጠሪያ ከፍተኛ ክትትል የተደረገበት በረራ እንደነበር ሲምፕል ፍላይት ዘግቧል።
ይሁንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሰላም ማረፍ መቻሉ ነው የተነገረው።
በጉዳዩ ላይ ዓየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ በረራውን የዓየር ትንበያን መሠረት በማድረግ ማከናወኑን ገልጿል።
በዚህም መሠረት አውሮፕላኑ በሚያርፍበት ሰዓት አውሎንፋሱ አለመኖሩን አስረድቷል።
በመሆኑም አውሮፕላኑ ያለምንም ችግር ማረፉን ገልፆ፥ ቀጥሎ ግን ዓውሎ ንፋሱ በአካባቢው በመድረሱና ለመነሳት አስቸጋሪ በመሆኑ የመልስ በረራውን ለሌላ ጊዜ ማዛወሩን ጠቁሟል።
በጉዳዩ ላይ የወጡ ዘገባዎች በተሳሳተ መንገድ መጠናቀራቸውን አየር መንገዱ ጠቁሟል።
#Ethiopia