በክልሉ የተጎዱ ት/ቤቶችን መልሶ ለመገንባት በልዩ ሁኔታ መረባረብ ይገባል- አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት እና ሁሉም አዲስና መደበኛ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ እንዲገኙ ለማድረግ በልዩ ሁኔታ መረባረብ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።
25ኛው ክልል አቀፍ የትምህርት ጉባኤ እና የ2016 የትምህርት ዘመን ንቅናቄ መድረክ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን÷ በክልሉ ባለፉት ዓመታት የነበረው የጸጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ጠቅሰው 287 የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መውደማቸውን ተናግረዋል።
ይህም ትምህርት መማር የነበረባቸውን ከ53 ሺህ በላይ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ አድርጓል ብለዋል።
ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ-ለመገንባት እና ሁሉም አዲስና መደበኛ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ እንዲገኙ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በልዩ ሁኔታ መረባረብ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
የክልሉ መንግስት ለዘርፉን አፈጻጸም ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ያሉት አቶ አሻድሊ ኃላፊነታቸውን በማይወጡ የዘርፉ አመራሮች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም መናገራቸውን ከክልሉ ርእሰ መስተዳድር ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አወቀ አይሸሽም(ዶ/ር) ንቅናቄው ሁሉንም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ 96 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው ባለድርሻ አካላትን በማሣተፍ እነዚህን ትምህር ቤቶች ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ይጠበቅብናል ብለዋል።