Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ  የሚኒስትሮች ጉባዔ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2023 የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ የሚኒስትሮች ጉባዔ በኬንያ ናይሮቢ ከተማ እየተካሄደ ነው።

መድረኩ ከአየር ንብረት  ለውጥ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በመጋፈጥ ረገድ አፍሪካ ያላትን ትልቅ አቅም ለማጎልበት ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተለይም ፍትሃዊ የአየር ንብረት የፋይናንስ ስርዓት መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ  ላይ ምክክር እንዲሚካሄድ የአፍሪካ ሕብረት መረጃ ያመለክታል።

በተጨማም የአየር ንብረት ለውጥ እና ከለውጡ ጋር የመጡ ጉዳቶች በዓለም ላይ በተለይም በአፍሪካ እያደረሱት ላለው ተጽዕኖ አፋጣኝ መፍትሔ ማበጀት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡

በ2016 በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ዱባይ በሚካሄደው 28ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በፊት አፍሪካ በጉባዔው ላይ የጋራ ድምጽ ማሰማት በምትችልበት ሁኔታ ላይም ጉባዔው ትኩረት እንደሚያደርግ ተጠቅሷል፡፡

በጉባኤው የተሳተፉት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)÷የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ጠቁመው÷ ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው አንስተዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነትንና ስኬትን በማብራራትም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም እና ስደትን ለማስቀረት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.