መንግስት የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቅረፍ እየሰራ ነው-ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቅረፍ ስትራቴጂ በመንደፍ ተግባር ላይ እያዋለ ነው ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) ገለፁ፡፡
የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በኬንያ ናይሮቢ ከተማ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን÷በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) በጉዳዩ ዙሪያ ሀሳባቸውን አካፍለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛ የእድገት ማነቆ እና የህብረተሰቡን ህልውና እየተፈታተነ ያለ ችግር መሆኑን መንግስት በመረዳትም ሀገራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅድ እና እ.አ.አ እስከ 2050 የሚተገበር የረጅም ጊዜ የአነስተኛ ካርቦን ልቀት እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የልማት ስትራቴጂ በመንደፍ ተግባር ላይ እያዋለ ነው ብለዋል፡፡
በተጨባጭ በተግባር እየዋሉ ካሉ መርሃ ግብሮች ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ አንዱ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ 25 ቢሊየን የደን፣ የመኖና ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ዝርያዎችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ራሷን በምግብ ለመቻል የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፍ ታስቦ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ተነሳሽነቱ ለጎረቤት ሀገራትም ትሩፋት መሆኑን ገልፀው ሁሉም ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት ሚኒስትሯ፡፡
ይሁንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የገንዘብ ስሪት እና መዋቅር ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት የሚያደናቅፍና ሀገራት በብድር አዙሪት ውስጥ እንዲቆዩ የሚያደርግ በመሆኑ ስር ነቀል የሆነ ለውጥ ሊደረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ÷ከነሃሴ 14 እስከ 18 ቀን 2023 በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ የተወሰኑ ውሳኔዎች አሁን በረቀቀውና የአፍሪካ የአየር ንብት ጉባኤ ዋና ውጤት ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው የናይሮቢ ዲክላዴሽን ውስጥ ግንዛቤ ውስጥ እንዲገባ ብሎም የ28ኛው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት አቋም ዋነኛ መነሻ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡