Fana: At a Speed of Life!

በሱዳን የጦር ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ሁለት የነዳጅ ኩባንያ ሥራ አስፈፃሚዎች ለፍርድ ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ20 ዓመታት በፊት በሱዳን በተፈፀመ የጦር ወንጀል ተባባሪ በመሆን የተከሰሱ ሁለት የስዊድን የነዳጅ ፍለጋና ማምረቻ ኩባንያ የስራ ኃላፊዎች የፍርድ ሂደት በስዊድን ስቶክሆልም ተጀምሯል።

የሉንዲን ኦይል ሊቀመንበር የነበሩት ኢያን ሉንዲን እና የቀድሞ ዋና ስራ አስፈፃሚ አሌክስ ሽናይተር በሱዳን የኦማር አልበሽርን መንግስት ይደግፉ ነበር ሲል ዐቃቤ ሕግ ተናግሯል።

ሁለቱ ሥራ አስፈፃሚዎች ለድርጅታቸው ጥቅም ሲሉ የሱዳን ወታደሮች እና አጋር ሚሊሻዎች ሰላማዊ ሰዎች ላይ ስልታዊ በሆነ መንገድ ጥቃቶች እንዲፈፀሙ አስፈላጊ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል ብሏል።

ዐቃቤ ሕግ ባወጣው መግለጫ ግለሰቦቹ በደቡባዊ ሱዳን ሰፊ ቦታ ላይ የነዳጅ ዘይት የመፈለግ እና የማውጣት መብትን በመጠቀም ለመክፈል እና ወደፊት ከሚገኘው ትርፍ ለመካፈል ስምምነት ላይ ተሳትፈዋል ብሏል፡፡

ክስ የቀረበባቸው ሉንዲን ክሱ ውሸት መሆኑን በመግለጽ “እራሳችንን በፍርድ ቤት እንከላከላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

በፈረንጆቹ ከ1983 እስከ 2005 ሱዳን በሰሜን እና በደቡብ በእርስ በእርስ ግጭት ስትታመስ መቆየቷ ይታወሳል።

በፈረንጆቹ 2003 በምእራብ ሱዳን በዳር ፉር በተቀሰቀሰ ግጭት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን÷ ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸውንም ቲ አር ቲ ወርልድ በዘገባው አስታውሷል።

ከዚህም በኋላ ደቡብ ሱዳን በፈረንጆቹ 2011 ከሱዳን በመነጠል ነፃነቷን አውጃ የዓለም ሀገራት ዝርዝር ውስጥ መቀላቀሏ ይታወቃል።

ዐቃቤ ሕግ የነዳጅ ኩባንያው ሃላፊዎች ለንግድ ሥራቸው ሲሉ ለፈፀሙት ወንጀል ሥራ አስፈፃሚዎቹ ለ10 ዓመታት ከንግድ እንቅስቃሴ እንዲታገዱ እና ኩባንያውም 3 ሚሊየን ክሮነር ወይም 227 ሺህ 250 ዶላር እንዲቀጣ ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም በዚሁ የጦር ወንጀል ምክንያት የሉንዲን ኦይል ኩባንያ ያገኘው 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ክሮነር ወይም 127 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ጥቅም እንዲወረስ መጠየቁ ተጠቁሟል፡፡

ችሎቱ በፈረንጆቹ 2026 መጀመሪያ ላይ ያበቃል የተባለ ሲሆን÷ ብይን የሚሰጥበት ቀን ግን በግልፅ አለመጠቀሱን ዘገባው አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.