በሲዳማ ክልል የአገልጋይነት ቀን “ኢትዮጵያን እናገልግል” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል ደረጃ የአገልጋይነት ቀን “ኢትዮጵያን እናገልግል” በሚል መሪ ሃሳብ በሀዋሳ ከተማ እየተከበረ ነው።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የስራ ሃላፊዎች እና ሰራተኞች ተገኝተዋል።
በዚህም የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ቀኑን አስመልክቶ በዓመቱ በስራቸው ምስጉን ለሆኑና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ባለሙያዎችና ተቋማት የእውቅናና ሽልማት የመስጠት መርሐ-ግብር እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
በስራቸው ውጤታማ ለሆኑ አገልጋዮች እውቅና መስጠት የአገልጋይነት ባሕልን በማዳበር ለሁለንተናዊ ለውጥ እንዲነሳሱ ፋይዳው የጎላ መሆኑም ተመላክቷል።
በተመሳሳይ በክልሉ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተሞችም የአገልጋይነት ቀን በተለያዩ መርሐ-ግብሮች እየተከበረ ነው።
ቀኑን በማስመልከትም ለከተማው ህብረተሰብ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በሲዳማ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የርዕዮተ-ዓለምና ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አስፋው ጓኔሶ÷ ከታክሲ አገልግሎት ጀምሮ በዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶች በተሻለ መልኩ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በብርሃኑ በጋሻው