Fana: At a Speed of Life!

በሲዳማ ክልል የበዓል ፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል የበዓል መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በተለያዩ የገበያ አማራጮች ለሕብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡

በቢሮው የንግድ ዘርፍ ሃላፊ ባቲሶ ኢዲሶ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በዘመን መለወጫ በዓል የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች እጥረት እንዳይፈጠር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በዚህ መሰረትም በክልሉ የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት፣ ዩኒኖች እና ነጋዴዎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በተመሳሳይ 70 በሚሆኑ የእሑድ ገበያዎች የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለሸማቹ ተደራሽ እየሆኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ጤፍ፣ ዱቄት፣ ሽንኩርት፣ ዶሮ፣ እንቁላል እና ሌሎች የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው ብለዋል፡፡

ለበዓሉ ከ920 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለሁሉም አካባቢዎች እየተሰራጨ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል 2 ሺህ 350 ኩንታል ስኳር ቢቀርብም ካለው ፍላጎት አንጻር አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለበዓሉ በቂ የእርድ እንስሳትን ለማቅረብ ትስስር መፈጠሩንም አብራርተዋል፡፡

ለበዓሉ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ችግር አለመኖሩን የገለጹት ሃላፊው÷ ነጋዴዎች አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ ኮሚቴ ተዋቅሮ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ለበዓል ገበያ ምርቶች ላይ ባዕድ ነገሮች እንዳይቀላቀሉ እና ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶች ለገበያ እንዳይቀርቡም ኮሚቴው ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.