የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ያስገነባውን የጀግኖች ማዕከል አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በግዳጅ ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው የፖሊስ አመራርና አባላት ያስገነባውን የጀግኖች ማዕከል አስመረቀ።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ማዕከሉን በይፋ መርቀው ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት ፥ ጀግኖቻችን ኢትዮጵያን ለማፅናት ሲፋለሙ አደጋ ሲያጋጥማቸው ከዚህ ቀደም የነበረው የፖሊስ ማስተናበሪያ ምቹ ያልሆነና አነስተኛ አገልግሎት የሚሰጥ እንደነበር አስታውሰዋል።
የማዕከሉን ሙሉ ወጪ ሸፍኖ በአንድ ዓመት ከስምንት ወር ውስጥ ግንባታውን አጠናቆ ላስረከበው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ምስጋና አቅርበዋል።
አያይዘውም ፥ አባቶቻችን ለሀገራችን በጀግንነት መስዋዕትነት ከፍለው በኩራት እንዳስረከቡን ሁሉ እኛም የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን በመመከት በመስዋዕትነት ጠብቀን ለትውልድ እናስረክባለን ብለዋል፡፡
የፖሊስ ሰራዊቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብራክ የወጣ በመሆኑ በሚንቀሳቀስበት ቦታ ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ሲያደርግ እንደነበረ ሁሉ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ነብዩ ዳኜ በበኩላቸው ለሀገራቸው ሲሉ ጉዳት ያስተናገዱ ጀግኖቻችን ዳግም ህይወታቸውን እየመሩ ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ የሚያደርግ የጀግኖች ማዕከል መገንባቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዮናስ አያሌው (ኢ/ር) በበኩላቸው ፥ ማዕከሉ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበት የተገነባ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ማዕከሉ ክሊኒኮች፣ የእንጨትና የብረታ ብረት ስራዎችን የሚሰሩበት ዎርክሾፕ፣ ጅምናዝየምና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች የሚያደረጉበት እንዲሁም ካፍቴሪያዎችን ማካተቱን አብራርተዋል።
ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን ከፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!