ሀገራችን መስዋዕትነት በሚከፍሉ ልጆቿ ለነገ ትውልድ ታፍራና ተከብራ ትሸጋገራለች – አቶ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራችን ትናትን በተከፈለ መስዋዕትነት ዛሬ ላይ እንደደረሰች ሁሉ መስዋዕትነት በሚከፍሉ ልጆቿ ለነገ ትውልድ ታፍራና ተከብራ ትሸጋገራለች ሲሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች “በመሥዋዕትነት የምትፀና ሀገር” በሚል መሪ ሐሳብ የመስዋዕትነት ቀንን በፓናል ውይይት፣ በስምሪት ላይ የተሰዉ አባላትን በመዘከርና በሌሎችም የተለያዩ መርሐ- ግብሮች አክብረዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በመርሐ -ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ዜጎች ለሀገራቸው የሚከፍሉት መስዋዕትነት በብዙ መልኩ ይይገለጻል።
የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ሥጋትን ቀድሞ በመለየትና በመተንተን ሊከፈል የሚችል አላስፈላጊ መስዋትነትን የማስቀረት ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያን ከድህነት ታሪክ ወጥታ ከፍ ብላ የምትታይ ሀገር በማድረግ ለነገው ትውልድ ለማስረከብ ሁሉም በተሰማራበት ሥራ ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ዕውቀቱን በማበርከት መስዋዕትነት መክፈል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት መጥፎ ሁኔታዎች ውስጥ ያሳለፈች ቢሆንም፤ መጪው አዲስ ዓመት ብሩህና የተሻለ ጊዜ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።
ታሪክ የሚያስረዳን እንደ ሀገር የገጠሙን ከባድ ፈተናዎች የታለፉት በአባቶች መስዋዕትነት ነው ያሉት ደግሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ፤ ኢትዮጵያ ፀንታ የኖረችው በመስዋዕትነት ነው ብለዋል።
በመሆኑም አገልግሎቱን የሚቀላቀል ዜጋ የመጨረሻውን መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ መሆኑ ከግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል።
የተከፈለን መስዋዕትነት ማክበር ለሌላው መስዋዕት ለመሆን ተነሳሽነትን የሚፈጥር በመሆኑ ጀግኖችን በአግባቡ ማክበርና ማሰብ ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ፤ በመርሐ ግብሩ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ሆን ተብሎ የሚሰራጩ የተዛቡ የታሪክ ትርክቶች ለሀገር መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች ተገቢውን ቦታ እንዳያገኙ እያደረገ በመሆኑ የእርምት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ጠቁሟል።