Fana: At a Speed of Life!

በበዓላት ወቅት የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመከላከል ዝግጅት ተደርጓል ተባለ

 

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በበዓላት ወቅት የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመከላከል ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ በመጪው አዲስ ዓመትና ቀጥሎ በሚከበሩ በዓላት ወቅት የኤሌክትሪክ ፍጆታ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

በተለይ አዲስ ዓመት በበርካታ ማህበረሰብ ዘንድ በሰፊው ስለሚከበር አደጋ ሊያጋጥም ይችላል ብለዋል፡፡

በዚህም የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበዓላት ወቅት የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቀነስና ለመከላከል የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

በዚህም በአደጋ ቅነሳ፣ የጥንቃቄ መልዕክትን የያዙ በራሪ ወረቀቶች ከነገ ጀምሮ በመዲናዋ በተመረጡ ቦታዎች በማሰራጨት የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶች እንደሚተላለፉ ጠቁመዋል፡፡

ከጥንቃቄው አልፎ አደጋ ሲከሰትም አደጋውን ለመቆጣጠር በሰው ሃይልና በአደጋ መቆጣጠር ማሽነሪዎች ዝግጅት መደረጉን ነው አቶ ንጋቱ ያስታወቁት፡፡

እንዲሁም ኮሚሽኑ ከፖሊስ፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም ከውሃና ፍሳሽ ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በበዓላት ወቅት ሁሉንም ስራዎች በተመሳሳይ ጊዜ የመስራት ፍላጎት፣ በማታ የበዓል ስራዎችን የማከናወን ፍላጎትና በድካም ስሜት ስራን የማከናወን ልምድ አለ በማለት ገልጸው፤ ይህም ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ አሰፈላጊዉ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት መክረዋል፡፡

እንዲሁም ከሰል እንደ አንድ የሀይል ፍጆታ ጥቅም ላይ ሲውል በሚገባ ተቀጣጥሎ በቂ አየር እንዲኖር በርና መስኮት ተከፍቶ እንደሆነ ገልጸው፤ ከተገለገልን በኋላ የከሰሉን እሳት ማጥፋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይ በአዲስ ዓመት አከባበር እና በመስቀል በዓል የደመራ እና ችቦ ማብራት ሥነ ሥርዓት ላይ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ሕዝቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባውም አሳስበዋል።

ወቅቱ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ የሚያመዝንበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችቦ አልበራ ሲል በነዳጅ ከማቀጣጠል መቆጠብ እና ችቦ የማብራት ስነስርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ማጥፋት እንደሚገባም አቶ ንጋቱ መክረዋል፡፡

እንዲሁም ሻማን እንደ ብርሃን ምንጭ ስንጠቀምም ሆነ እንደ በዓል ማድመቂያ ስንጠቀም ጥንቃቄ መደረግ እንደሚባ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ አልፎ ለሚከሰት አደጋ ጥቆማ ለመስጠት 939 ወይም 0111555300 ስልክ ቁጥሮችን መጠቀም እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.