የበጎነት ቀንን አስመልክቶ በኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር ፅ/ቤት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጳጉሜን 3 የበጎነት ቀንን አስመልክቶ በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ፅ/ቤት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
መድረኩ በቡሳ ጎኖፋ፣ በኦሮሚያ ገንዘብ ቢሮ እና በክልሉ ርዕስ መስተዳድር ፅ/ቤት እንደተዘጋጀ ተገልጿል፡፡
በውይይቱ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ፅ/ቤት ኃላፊ ሞገስ ኤደኤ፣ የቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ ሃብታሙ ሲሳይ፣ የኦሮሚያ የዜግነት አገልግሎት ኃላፊ መሀመድ ናስር አባጀማል (ዶ/ር) እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳትፈዋል።
የውይይት መድረኩን የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ፅ/ቤት ኃላፊ ሞገስ ኤደኤ÷በጎነት የገዳ ስርዓት አካልና የኦሮሞ ሕዝብ ጥንታዊ ዕሴት ነው ብለዋል፡፡
እየደበዘዘ የነበረውን የመረዳዳት ዕሴት የቡሳ ጎኖፋ ስርዓትን በመገንባት ማጎልበት መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡
ይህንንም ቀን በጎ ከማሰብ ባለፈ መልካም ነገርን በማድረግ ልናሳልፈው ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የክልሉ የዜግነት ኃላፊ መሀመድ ናስር አባጀማል (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ባለፉት ዓመታት በክልሉ በዜግነት አገልግሎት በርካታ በጎ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡
ለ2016 በጀት ዓመት በዜግነት አገልግሎት ከ102 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ተግባር ለመፈፀም ታቅዶ ከወዲሁ ከ28 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የበጎ ተግባር መፈፀም መቻሉንም ተናግረዋል።
በዚህ መድረክ በጎነትን የተመለከቱ ሶስት ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት እየተካሄደባቸው ይገኛል።
በመራኦል ከድር