Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን አየር ኃይል የመገንባት ስራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል – ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ዘመናዊና አስተማማኝ አየር ኃይል የመገንባት ስራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በተቋሙ ለረጅም ዓመታት ላገለገሉና የላቀ አፈጻጻም ላሳዩ ከፍተኛ መኮንኖች የማዕረግ እድገት ሰጥቷል።

የአየር ኃይል ለከፍተኛ መኮንኖችና አመራሮች የሜዳሊያ፣ ሪቫንና የምስክር ወረቀት የመስጠት መርሐ-ግብርም አካሄዷል።

በዚሁ መሰረት ተቋሙን ከ25 እስከ 35 ዓመት ላገለገሉ አምስት ከፍተኛ መኮንኖች በየደረጃው የውትድርና አገልግሎት ሜዳሊያና ሪቫን እንዲሁም ሰርተፊኬት ተሰጥቷል።

በተጨማሪም የመቆያ ጊዜያቸውን ለሸፈኑ እንዲሁም በሰራዊቱ መተዳደሪያ ደንብ የማዕረግ አመላመል ስርዓትን መሰረት በማድረግ መስፈርቱን ላሟሉ 585 መኮንኖች የማዕረግ እድገት ተሰጥቷቸዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ ተቋሙ በሰው ኃይልና ተቋም ግንባታ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በተያዘው ዓመት ወታደራዊ አቅምን የማጎልበት እንዲሁም በአስተሳሰብና በሙያ የሰው ኃይሉን ማብቃት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ዘመናዊና አስተማማኝ አየር ኃይል የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያን እኛ እያለን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ማንም ሊደፍራት አይችልም ያሉት ጄኔራሉ፤ በመጪው ዓመት በተሻለ ግዳጅ አፈጻጸም ተቋማዊ ስኬት ለማምጣት እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።

የማዕረግ እድገት የተሰጣቸው የሰራዊቱ አባላት ኢትዮጵያን በላቀ ትጋት እንዲያገለግሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የማዕረግ እድገት ያገኙ የሰራዊቱ አባላት በበኩላቸው የተሰጠን የማዕረግ እድገት ለቀጣይ ግዳጅ አፈጻጸም ከፍተኛ መነሳሳት የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የአየር ኃይል የበጎነት ቀንንና የዘመን መለዋጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ በቅጥር ግቢው አምርቶ ያዘጋጀውን የስንዴ ዱቄት ከቢሾፍቱና አካባቢው ለተወጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች አበርክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.