አቶ አረጋ ሀገራዊ ምክክሩ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ መደላድል እንደሚፈጥር ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባላት ጋር ተወያይተዋል።
አቶ አረጋ ከበደ ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩ የተሳሳቱ ትርክቶች በሕዝብ አንድነት ላይ አደጋ የሚጥሉ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
የአማራ ሕዝብም የተሳሳቱ የፖለቲካ ትርክቶች ታርመው በምክክር ወደ ተሻለ ሀገረ መንግሥት ግንባታ እንዲገባ በተለያዩ አጋጣሚዎች እያነሳ መቆየቱን አንስተዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተረጋጋችና የምንፈልጋትን ጠንካራ ኢትዮጵያ ለመገንባት ትልቅ መደላድል ለመፍጠር አጋዥ እንደሚሆን ትልቅ እምነት አለን ብለዋል።
በአብሮነት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረገው የምክክር ሒደት በውጤታማነት እንዲከናወንም የክልሉ መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥርም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ ኮሚሽኑን በሰው ሃይል ከማደራጀት ጀምሮ ለሀገራዊ ምክክሩ በአጀንዳነት የሚመረጡ ርዕሰ ጉዳዮችን እያሰባሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በየወረዳው ሰባት ተባባሪ አካላትን እንፈልጋለን ያሉት ኮሚሽነሩ÷ ከዘጠና እስከ አንድ መቶ ሰዎችም ይለያሉ ነው ያሉት።
ሊካሔድ በታሰበው የምክክር ሒደት የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ግብዓት እንዲያመቻች መጠየቃቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡