የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተቋማዊ አደረጃጀት ተፈጥሮለታል – የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ዘርፉን በዘላቂነት እንዲደግፍ ተቋማዊ መዋቅር እንዲዘረጋለት መደረጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በንቅናቄው የአገር ውስጥ አምራቾች ምርታማነት ላይ ለውጦች መታየታቸውንና ባለሀብቶች በዘርፉ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎታቸው መጨመሩን ገልጸዋል።
በተለይም ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በተደረጉ ውይይቶች የመሬት አቅርቦት ዋንኛው ችግር መሆኑ ተለይቶ በተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች ለውጦች መታየታቸውን አመልክተዋል።
በንቅናቄው በፋይናንስ፣ በግብአት አቅርቦት፣ በወሰን ማስከበርና ሌሎች ችግሮች ስራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ የመመለስ ተግባር በትኩረት መከናወኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከ350 በላይ ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ማምረት መመለሳቸውን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የጠቆሙት።
በንቅናቄው የኢንዱስትሪው ዘርፍ የማምረት አቅም በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 55 በመቶ እንዲያድግ ማስቻሉን ገልጸዋል።
የውጭ ምንዛሬ ማስገኘትና ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል አቅም መፍጠሩንም አመልክተዋል።
በንቅናቄው የጸጥታ አካላት የደንብ ልብስን በሀገር ውስጥ በማምረት 60 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን በማሳየነት ጠቅሰው፤ የተማሪዎች ዩኒፎርም እየተመረተ እንደሚገኝም አክለዋል።
የምግብ፣ የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ዘርፎች በንቅናቄው የተሻለ ለውጥ ከታየባቸው ዘርፎች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።
ንቅናቄው ወደ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤትነት አድጎ ግብርና፣ ኢንቨስትመንት፣ መሰረተ ልማትና ግብአትን ጨምሮ በዘርፉ ያለውን ምርታማነት ለማሳደግ ክላስተሮች ተቋቁመው ወደ ስራ ገብተዋል ብለዋል።
በዚህም አምራቾች በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሪ ከማዳን ባለፈ ምርታማነትን እየጨመሩ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአምራች ኢንዱስትሪውን እድገትና ተወዳዳሪነትን የማሳደግና አምራቾችን በብዛትና በጥራት የማፍራት ዓላማ ያለው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚያዚያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!