Fana: At a Speed of Life!

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ተመዘገበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ቅርስ ኮሚቴ የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ውሳኔ አሳልፏል።

በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጰያ ሁለተኛው በዓለም ደግሞ 11ኛው ታላቅ የተፈጥሮ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል።

45ኛው የዓለም የቅርስ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ሁለት ታላለቅ የቱሪስት መዳረሻዎችን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ መቻሏ ተገልጿል፡፡

የባሌ ተራራዎች ብሄራዊ ፓርክ በ 1962 ዓ.ም ተቋቋመ ሲሆን÷ የቆዳ ሥፋቱ 2 ሺህ 150 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ይሸፍናል፡፡

የመሬት ከፍታው ከባሕር ጠለል በላይ ከ1 ሺህ 500 እስከ 4 ሺህ 377 ሜትር የሚደርስ ሲሆን÷ በውስጡም የኢትዮጵያ ሁለተኛ ትልቁ ተራራ ቱሉ ዲምቱ ይገኛል፡፡

በፓርኩ የተለያዩ ብርቅዬ የእፅዋት እና የዱር እንሥሣት ዝርያዎች እንደሚገኙም የቱሪዝም ሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በብሔራዊ ፓርኩ ውስጥ በጥናት ከተለዩት 1 ሺህ 660 የእጽዋት ዝርያዎች ውስጥ 40 በመቶ የመድሃኒትነት ፋይዳ ያላቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

177 የሚሆኑት የእጽዋት ዝርያዎችም በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡

በትናንትናው ዕለትም በጌዴኦ ዞን የሚገኘው የጌዴኦ ባሕላዊ መልክዓ- ምድር በዩኔስኮ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.