Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል 1 ሚሊየን የሚጠጉ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በዝናብ እጥረት ምክንያት 1 ሚሊየን የሚጠጉ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ÷ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት መከሰቱን ተናግረዋል፡፡

በክልሉና ከሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉ ከ1 ሚሊየን በላይ ወገኖች መኖራቸውን ጠቅሰው÷ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች ድርቅ እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ዞን አራት ወረዳዎች የዝናብ እጥረት መከሰቱንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተደር በሰሃላ ሰየምት ወረዳ የከፋ ችግር መኖሩን አንስተው÷ በክልሉ በድርቁ ምክንያት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቁጥር 1 ሚሊየን መድረሱንም ነው የገለጹት፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተተዳደር የዝናብ እጥረት ተከስቷል ያሉት ኮሚሽነሩ÷ ሰሜን ሸዋ ላይም በግሪሳ ወፍ ወረራ ምክንያት ችግር መኖሩን አስታውቀዋል።

ዓለም ዓቀፍ ረጂ ድርቶች ድጋፍ ማቆማቸውን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፥ የክልሉ መንግሥት ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

መንግሥት በመጠለያ ለሚኖሩ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ነው የተባለ ሲሆን÷ በጸጥታ ችግር ምክንያት ድጋፍ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች መኖራቸውም ተጠቅሷል፡፡

እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ ርብርብ እንደሚያስፈልግም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.