Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገኘውን ሠላም በማጽናት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

የክልሉ የከፍተኛ አመራሮች ቡድን በመተከል ዞን ያካሄደውን የስምሪት አፈጻጸም ርዕሰ መስተዳድሩ ከሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ገምግመዋል።

በመድረኩም በመተከል ዞን አጠቃላይ የሠላሙ ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ ተገልጿል፡፡

ሙሉ በሙሉ ሠላም በሆኑ አካባቢዎች የግብርና ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑም ነው የተነገረው።

ባለፉት ዓመታት በሠላም እጦት ውስጥ ከነበሩ አካባቢዎች አንዱ በነበረው የመተከል ዞን የታየውን ሠላምና ልማት የበለጠ ለማጠናከር አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡

ሠላም በዞኑ ሁሉም አካባቢ እንዲረጋገጥም እስከ ታችኛው መዋቅር የተጠናከረ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መሥራት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

መንግስት ያቀረበላቸውን የሠላም አማራጭ ተቀብለው ኅብረተሰቡን ለመቀላቀል የሚመጡትን የተሐድሶ ሥልጠና በመሥጠት ወደ ልማት ለማስገባት ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በክልሉ አሁን የተገኘውን ሠላም ለማምጣት ትናንት የከፈልነውን መስዋዕትነት መርሳት የለብንምም ነው ያሉት አቶ አሻድሊ፡፡

የቀረበላቸውን የሠላም አማራጭ ገፍተው ወደኋላ ለመመለስ የሚሰሩ አካላት ላይ ግን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ መገለጹን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.