የሀረሪ ክልል የቱሪዝም ብራንድና አርማ የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ ለማስተዋወቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል -ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀረሪ ክልል የቱሪዝም ብራንድና አርማ የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ ለማስተዋወቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ኦርዲን በድሪ ገለፁ፡፡
ርዕሰ መስተዳደሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት “ሀረር ህያዊቷ ሙዚየም” የተሰኘው የሀረሪ ክልል የቱሪዝም ብራንድና እና አርማ ይፋ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ይህ አዲሱ የሀረሪ ክልል የቱሪዝም ብራንድና እርማ የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ ከማስተዋወቅ አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
በጁገል አለም አቀፍ ቅርስ ዙሪያ ማራኪ የመስህብ ቦታዎች እንዲለሙ መደረጉ ክልሉ የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ የነዋሪዎቿ የኩራት ምንጭ ለመሆን መብቃቱን አንስተዋል።
ሀረርን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ረገድ የቱሪዝም ልማትና ተጠቃሚነትን በማሳደግ ክልሉን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንሚቀጥሉ ገልፀዋል።