Fana: At a Speed of Life!

በዲፕሎማሲ የታየው ስኬት ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ያላትን የተገቢነት ቦታ ዳግም ያረጋገጠ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዲፕሎማሲ መስክ የታየው ስኬት ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ያላትን የተገቢነት ቦታ ዳግም ያረጋገጠ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ንጋት ከድምጽ አሰሚነት ወደ ተሰሚነት መሸጋገሩን አውስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መዝገብ ሲገለጥ የሚነበበው በክብር የቆመ የታሪክ መሠረት ነገር ግን እንደ ጥንታዊነቷ ድምጿ ጎልቶ የማይሰማበት የቆየ አሠራር እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተመዘገበው ድል ግን ይሄንን የተገደበ ተሳትፎ በመስበር ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ መድረክ ዋነኛ ተዋናይ ያደረገ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል ነው ያሉት፡፡

የለውጡ መንግሥት ዲፕሎማሲን እንደ ሀገራዊ ሉዓላዊነት መጠበቂያ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ብልጽግና ምንጭ በመቁጠር በብርቱ መስራቱን ጠቁመዋል።

ዛሬ የዚህ ብልህ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ፍሬ እያፈራ የሰላም እና የትብብር ጥረቱ አዝመራ እየታጨደ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ለዚህ ሥር ነቀል ለውጥና ኢትዮጵያን በጎረቤት ሀገራትና በአህጉር ደረጃ ያላትን አቀራራቢ ሚና በማጠናከር የቀጣናውን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ የነበረውን የቆየ እሳቤ መቀየር መቻሉን ጠቅሰዋል።

ሀገርን ማዕከል ያደረገ፣ ክብሯን እና ጥቅሟን የሚያስከብር ተለዋዋጭ ዲፕሎማሲ በመከተል ለተገኘው ስኬት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቁልፍ መሐንዲስ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ መቀላቀል፣ በአፍሪካ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት መድረኮች ላይ የሚቀነቀነው አቋሟ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መሪዎች ዘንድ ያገኘችው ከፍ ያለ ተቀባይነት የዚሁ የጠራ ራዕይ ውጤት እንደሆነ አብራርተዋል።

ዛሬ በዲፕሎማሲው መስክ እያየን ያለነው ስኬት ሁሉ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ያላትን የተገቢነት ቦታ ዳግም ያረጋገጠ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.