አቶ አሻድሊ ሀሰን ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 26 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ለኢሬቻ በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ አሻድሊ ሀሰን በመልዕክታቸውም የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ሕዝብ በአንድነት ወጥቶ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበትና አብሮነትን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
የኢሬቻ በዓል የይቅርታ፣ የሠላም የፍቅር እና የአብሮነት በዓል መሆኑን የገለጹት አቶ አሻድሊ፥ ጨለማው አልፎ ብርሃን፣ የችግር ጊዜ አልፎ ደስታ እና ተስፋ መተካቱን የሚዘከርበት፣ ይህንን ላደረገ ፈጣሪም ከቂምና ከበቀል ነጻ ሆኖ ምስጋና የሚቀርብበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ዘመናትን የተሻገረው የኢሬቻ በዓል አብሮነትና ጥላቻ፣ ቂም፣ መገፋፋት እንዲከስም በአንጻሩ ደግሞ ወንድማማችነትና አብሮነት የበለጠ እንዲጎለብት እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የኦሮሞ ሕዝብ ከመላው የሀገራችን ሕዝቦች ጋር በጋራ የሚያከብረው የኢሬቻ በዓል ለሀገራችን ኢኮኖሚና ቱሪዝም ዕድገት ያለው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ፥ በዓሉ የበለጠ እንዲተዋወቅና በአግባቡ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር በጋራ መስራት እንደሚገባም አቶ አሻድሊ ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና የኦሮሚያ ክልል ሕዝቦች ለዘመናት የገነቡትን አብሮነት የበለጠ አጠናክሮ ከማስቀጠል ባለፈ፥ ሕዝቦቹን በሠላምና ልማት ለማስተሳሰር እየተከናወኑ የሚገኙ ተጨባጭ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
ኢሬቻ ሠላም፣ ይቅርታ፣ መተባበርና ወንድማማችነት መገለጫው ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የዘንድሮው በዓልም ይህንን ዕሴቱን ጠብቆ በሠላም እንዲከበር የሁሉም ኃላፊነት ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የኢሬቻ በዓል ለመላው የኦሮሞ ሕዝብና ኢትዮጵያውያን የሠላም፣ የፍቅር፣ የደስታና የአብሮነት በዓል መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።