የ2016 ሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ ተከበረ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 26 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2016 ሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል እሴቱን በጠበቀ መንገድ በአዲስ አበባ በልዩ ልዩ ሁነቶች ተከበረ።
የኢሬቻ በአል እንደ ሁልጊዜው የኢትዮጵያን ባሕል እና መልካም እሴቶች በውበትና በድምቀት ለተቀረው ዓለም በሚያንፀባርቅ መልኩ ነው የተከበረው።
ጸብ በይቅርታ የሚሻርበት፣ የሰላም፣ የአንድነት እና የወንድማማችነት አርማ የሆነው ይህ በዓል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ነው የተከበረው።
በዓሉ ሌሊት ላይ በገዳ ስርዓት መሰረት በአባገዳዎች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን፥ የበዓሉ ተሳታፊዎችም ከሌሊት ጀምሮ በስፍራው ተገኝተው በዓሉን እያከበሩ ይገኛሉ።
የበዓሉ ታዳሚዎች በዓሉን በሚገልጹ ባህላዊ አልባሳት በመዋብ ባህላዊ ክዋኔዎችን በጋራ እየፈፀሙ በቡድን ሆነው ባህላዊ ዜማዎችን በመጫወትና ደስታቸውን በመግለፅ በአንድነት መንፈስ አክብረዋል።
የበአሉ ታዳሚዎች ከዘመን ዘመን ላሸጋገራቸው አምላክ ምስጋናን አቅርበዋል።
በመራኦል ከድር