ለ500 ሺህ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ለመፍጠር እንደሚሰራ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት በ5 መዳረሻ ሀገራት ለ500 ሺህ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ለመፍጠር እንደሚሰራ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንቷ በተያዘው በጀት ዓመት ትኩረት በሚደረግባቸው ጉዳዮች ላይ በሰጡት ማብራሪያ÷ከውጭ ሃብት ግኝትና ፍሰት በበጀት ዓመቱ 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለማግኘት ታስቧል ብለዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም በሕጋዊ መንገድ በ5 የመዳረሻ ሀገራት ለ500 ሺህ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ለመፍጠር እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በትምህርት ዘርፍ ላይ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶች መሰረት እንዲይዙ የሚደረገው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡
እንዲሁም በጤናው ዘርፍ የእናቶች የወሊድ ጤናማነትና የመቀንጨር መጠንን የመቀነስ ተግባር ዋነኛ የትኩረት ማዕከል ሆኖ ይሰራል ብለዋል፡፡
ውስጣዊ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድና በውይይት ብቻ እንፍታ ያሉት ፕሬዚዳንቷ÷አርበኛ ትውልድ እንሁን፣ ትብብራችን ለወንድማማችነትና ለአብሮነት ይሁን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ዓርበኛ ትውልድ ጥላቻን እንደሚጸየፍና ፍቅርን እንደሚያንጽ ገልጸው÷ መከፋፈልን በማስወገድ፣ ትብብርን አንደሚያነግስ እና ፈተናዎችን ወደ እድል ቀይሮ ሀገራዊ እድገትን እንደሚያስመዘገብም አስረድተዋል፡፡
በየሻምበል ምህረት