የግሪሳ ወፍ ወረራን ለመከላከል የተካሄደው የኬሚካል ርጭት ከ98 በመቶ በላይ ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 29 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የግሪሳ ወፍ ወረራ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የተካሄደው የኬሚካል ርጭት ከ98 በመቶ በላይ ውጤታማ ነው ሲል የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በክልሉ የግሪሳ ወፍ ወረራን ለመከላከል አሁንም እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ በምሥራቅ አማራ አካባቢዎች የግሪሳ ወፍ ወረራ መከሰቱን አስታውሰዋል፡፡
በክልሉ የግሪሳ ወፍ ወረራ በተከሰተባቸው ዋና ዋና ቦታዎች እና የግሪሳ ወፍ ማደሪያ በሆኑ ቦታዎች ላይም በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በአውሮፕላን የታገዘው የኬሚካል ርጭት ከ98 በመቶ በላይ ውጤታማ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የኬሚካል ርጭት የሚያደርገው አውሮፕላን አንድ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፥ አውሮፕላኑ ወደ ሌሎች ክልሎች ለኬሚካል ርጭት እንደሚሄድም ነው የጠቀሱት።
አውሮፕላኑ ዳግም እስከሚመለስ በባሕላዊ መንገድ ያለውን የመከላከል ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የሰላም እጦቱ በሰብል ጥበቃ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን በማንሳትም ማኅበረሰቡ የግሪሳ ወፉን በመረበሽ እና ሌሎች ባሕላዊ የመከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም መከላከል እንደሚገባ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!