አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸው አምባሳደር ምስጋኑ ሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው ወደሚችል ጠንካራ አጋርነት ለማሳደግ በቅርበት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በትምህርትና ንግድ ዘርፍ የትብብር መስኮች ማሳደግ ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተም ማብራሪያ ሰሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያና የቼክ ሪፐብሊክን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህ ረገድም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ እንደሆኑ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በሌላ በኩል አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ ከባንግላዴሽ አምባሳደር ስኪደር ቦዲሩዛማን ጋር ባደረጉት ውይይት÷ የሁለትዮሽ ትብብርን በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ እና በባለብዙ ወገን መድረኮች ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በዳካ ኤምባሲዋን ለመክፈት ፍላጎት እንዳለትም አምባሳደር ምስጋኑ በውይይታቸው ላይ ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ቦዲሩዛማን በበኩላቸው÷ መንግስታቸው የንግድ ግንኙነቱን ለማሳደግ እና የአየር ትራንስፖርት ትስስርን ለማመቻቸት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።