ኤጀንሲው የ9 ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት አካሄደ
አዲስ አበባ፣ግንቦት 9፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) የ2012 የ 9 ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
በሪፖርት ውይይቱ ላይ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር እና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች እንዲሁም የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት መደረጉም ነው የተገለጸው።
በሪፓርቱ ላይ ኤጀንሲው በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን ማድረጉ፣ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡና በሚወጡ የቴክኖሎጂ ምርቶች ላይ ቁጥጥር ማከናወኑ፣ በሀገሪቱ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል እንዲሁም የተቋማትን አሰራር በማዘመን በኩል ፋይዳቸው ከፍተኛ የሆኑ ሥራዎችን ባለፉት 9 ወራት ማከናወን መቻሉ ተብራርቷል።
ከዚያም ባለፈ ኤጀንሲው የተቋሙን ቀጠናዊ እና አለም አቀፋዊ ተጽእኖ ፈጣሪ እንዲሆን ከማድረግ አንጻር በተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው የተዘጋጀ ቴክኖሎጂ ዴቨሎፕመንት እና ፕሮዳክት ኮሜርሻይሌዜሽን ̋ በሚል አዲስ ሮድ ማፕ ይፋ ተደርጓል።
ዋና ዳይሬክተሩ በቀጣይም በዚሁ ሮድ ማፕ ዙሪያ ሰፊ ውይይት በማድረግ በተጨማሪ ሀሳቦች እንዲዳብር ይደረጋል ብለዋል።
አያይዘውም ቀጣይነት ባለው መልኩ ተቋሙ ለሚያከናውናቸው ተልእኮ ተኮር የፈጠራ እና የምርምር ስራዎች ላይ አባላት እና አመራሩ የሚኖራቸው ሚና የላቀ መሆኑን በመገንዘብ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ዋና ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ከኢመደኤ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።