የወባ ሥርጭትን ለመቆጣጠር ዜጎች የመከላከያ መንገዶችን በትክክል ሊተገብሩ ይገባል – ዶ/ር ሊያ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የወባ ሥርጭት ለመቆጣጠር ዜጎች የወባ መከላከያ መንገዶችን በትክክል ሊተገብሩ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ፡፡
5ኛው ሀገር አቀፍ የወባ ሳምንት “ወባን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል“በሚል መሪ ሃሳብ በአሶሳ ከተማ ተከብሯል፡፡
በመድረኩ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ዶ/ር ሊያ በ2015 በጀት ዓመት የወባ ሥርጭትን ለመከላከል በ537 ወረዳዎች 19 ነጥብ 7 ሚሊየን የአልጋ አጎበር መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም 40 ሚሊየን ዜጎች የአጎበር ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው÷አንድ ሚሊየን ቤቶች ላይ የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት መካሄዱንም ጠቅሰዋል፡፡
ሁሉም ዜጋ የአልጋ አጎበር መጠቀምና መኖሪያ ቤቱን በፀረ ወባ ኬሚካል በማስረጨት ስርጭቱን መቀነስ እንደሚገባም ዶ/ር ሊያ አሳስበዋል።
አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው÷የወባ በሽታ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ሁለንተናዊ ጉዳት ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡