ናይጄሪያ የነዳጅ ምርቷን በቀን ወደ 2 ሚሊየን በርሜል ከፍ ልታደርግ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ናይጄሪያ የነዳጅ ምርቷን በቀን ወደ 2 ሚሊየን በርሜል ከፍ ልታደርግ መሆኑን አስታውቃለች፡፡
በአቡጃ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በሰባት አዳዲስ ደንቦች ላይ ለአንድ ሳምንት ያህል የቆየ ውይይት አድርገዋል፡፡
የናይጄሪያ የላይኛው ተፋሰስ ቁጥጥር ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ግቤንጋ ኮምላፌ እንደተናገሩት ፥ በተያዘው ዓመት መጨረሻ ላይ በቀን 2 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ ለማምረት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
ከመካከለኛ እስከ አጭር ጊዜ በተቀመጠው እቅድ መሰረትም በቀን የሚገኘውን የነዳጅ ምርት ወደ 4 ሚሊየን በርሜል ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ነው የገለጹት፡፡
ሀገሪቱ አሁን ለይ በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ የምታመርተው ነዳጅ በቀን 1ነጥብ 3 ሚሊየን በርሜል መሆኑ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
የሌጎስ የንግድ ም/ቤት የነዳጅ አምራች ንግድ ክፍል ተወካይ ናታኒኤል ኦያቶገን በበኩላቸው፥ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያሻሽል ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር የቁጥጥር ስርዓቱን ማሻሻልእንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ።
ማሻሻያ የሚደርግባቸው የቁጥጥር ሥርዓቶች ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውንም ዘ ጋርድያን ዘግቧል፡፡