Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ለሥራው መሳካት የሰላምና ዲፕሎማሲ ጉዳይን አጠንክሮ መያዝ ይኖርበታል – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ስራዎቹ የተሳኩ እንዲሆኑ በቀጣናዉ ያለዉን የሰላምና ዲፕሎማሲ ጉዳይ አጠንክሮ መያዝ ይገባል ሲሉ ምሁራን ገለጹ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራኑ የባህር በር ስራዎችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በንግግር መስራትም ኢትዮጵያ የምትፈልገዉን ለማግኘት ያግዛታል ብለዋል፡፡
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ደህንነትና ጥናት መምህርና ተመራማሪ ተመስገን ቶማስ (ዶ/ር) የባህር ኃይል መደራጀት ጥቅሞቹ ብዙ ናቸዉ ይላሉ፡፡
በኢኮኖሚ ትስስር እንዲኖርና የጋራ ደህንነትን በጋራ ከመጠበቅ አንጻር የባህር በር መኖሩ ሚናዉ የጎላ እንደሆነም ነዉ ያነሱት፡፡
የባህር ኃይል አደረጃጀቱ የባህር በር ስራዎችን ለመስራት ነዉ የሚሉት የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ደያሞ ዳሌ በበኩላቸው፤ አቅም ያላቸዉ ሀገራት በሙሉ በዚህ ላይ ይሰራሉ ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያን የወጪ ንግድም ለመቆጣጠር ቀይ ባህር አካባቢ ያለዉን እንቅስቃሴም ለማጤን የባህር ኃይሉ ተግባር ከፍተኛ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለመነጋገር የሚያስችሉ በርካታ ምክንያቶች በመኖራቸው ለጋራ ልማትና ሰላም እንዲሁም ደህንነት ሲባል የዲፕሎማሲዉን መንገድ አጥብቆ መያዝ ያስፈልጋል ሲሉም ምሁራኑ አክለዋል፡፡
በሃይማኖት ወንድራድ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.