Fana: At a Speed of Life!

ዋሽንግተን እስራኤል በጋዛ ለማካሄድ ያሰበችውን የምድር ላይ ዘመቻ እንድታዘገየው ጫና መፍጠሯ ተሰማ

 

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 10 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ እና አንዳንድ አጋር ሀገራት እስራኤል በጋዛ ለማካሄድ ያሰበችውን የምድር ላይ ዘመቻ እንድታዘገየው ጫና እያደረጉ መሆኑ ተሰማ።

ብሉምበርግን ዋቢ ያደረገው የአር ቲ ዘገባ ዋሽንግተንና የተወሰኑ የአውሮፓ አጋር ሀገራት ቴል አቪቭ በምድር ላይ አካሂደዋለሁ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ በሃማስ የተያዙ ታጋቾችን ማስለቀቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመደራደር በማሰብ እንድታዘገየው እየወተወቱ መሆኑን አስነብቧል።

እስራኤል በሃማስ ለተፈጸመብኝ ጥቃት ከባድ አፀፋዊ ምላሽ እሰጣለሁ በሚል በጋዛ ከአየር ጥቃት ባለፈ በቅርቡ የተጠናከረ የምድር ላይ ዘመቻ አደርጋለሁ ማለቷ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ አሜሪካ እና አንዳንድ አጋር ሀገራት ታጋቾችን በድርድር ለማስለቀቅ እስራኤል ዘመቻዋን እንድታዘገየው ጠይቀዋል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት ውሳኔያቸው በጋዛ የሚገኙ ታጋቾችን ለማስለቀቅ የሚያስችል “ጊዜ ማግኘት” ያስቸለናል የሚል እምነት እንዳላቸውም ነው ዘገባው የሚያመላክተው።

ሃማስ ባለፈው የፈረንጆቹ ጥቅምት 7 በእስራኤል ከፈጸመው ጥቃት በኋላ አሜሪካውያንን ጨምሮ ከ200 በላይ ሰዎችን መያዙ ይታወሳል።

አሜሪካም በኳታር አማካኝነት ታጋቾችን ለማስለቀቅ “ሚስጥራዊ” የተባለ ድርድር እያደረገች መሆኑን ብሉምበርግን ዋቢ ያደረገው የአር ቲ ዘገባ ያመላክታል።

እንደዘገባው ከሆነ ሌሊቱን እናትና ልጅ አሜሪካውያን ከእገታ የተለቀቁ ሲሆን፥ አሁን ላይም በእስራኤል መከላከያ ክትትል እየተደረገላቸው ነው።

የድርድሩ አንድ አካል የሆነውን የታጋቾችን መለቀቅ ያሞካሸው የኳታር ውጭ ጉዳይ በበኩሉ ተጨማሪ ውይይቶች ይቀጥላሉ ብሏል።

ሃማስ ከሁለት ሳምንት በፊት እስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመ ወዲህ እስራኤል በጋዛ ተከታታይ የአየር ጥቃት መፈጸሟ ሲነገር ቆይቷል።

ይህን ተከትሎም ተመድና ሰብአዊ ድርጅቶች በአካባቢው የከፋ ሰብአዊ ቀውስ እንዳይደርስ በማሰብ የተኩስ አቁም እንዲደረስና የሰብአዊ ኮሪደር መተላለፊያ እንዲኖር ጠይቀዋል።

በእስራኤል ሃማስ ግጭት እስካሁን ከ5 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

እስካሁን ከ4 ሺህ 100 በላይ ፍልስጤማውያን እና ከ1 ሺህ 400 በላይ እስራኤላውያን ለህልፈት መዳረጋቸውን የጤና ተቋማትን ሪፖርት ዋቢ አድርጎ ዘገባው አስነብቧል።

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.