ፍርድ ቤቱ በጋምቤላ ክልል ተፈጽሟል ከተባለ የንፁሀኖች ግድያ ጋር ተያይዞ 15 ተከሳሾች ላይ የዓቃቤ ህግ የምስክር ቃል መስማት ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ በጋምቤላ ክልል ተፈጽሟል ከተባለ የንፁሀን ዜጎች ግድያ ጋር ተያይዞ የተከሰሱ የጋምቤላ ክልል የቀድሞ የፖሊስ ኮሚሽነሮችና የልዩ ኃይል አዛዦችን ጨምሮ በ15 ተከሳሾች ላይ የዓቃቤ ህግ የምስክር ቃል መስማት ጀመረ።
ተከሳሾቹ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ተከትሎ ነው የዓቃቤ ህግ ምስክር ቃል መሰማት የተጀመረው።
ምስክር ቃል መስማት የጀመረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቡላ ኦባንግ፣ ም/ኮሚሽነር የነበሩት ቱት ኮር፣ የክልሉ የልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር የነበሩት ኮንግ ሬክና የክልሉ ልዩ ኃይል ምክትል አዛዥ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር ኡጀዲ ባሬን እንዲሁም የተለያዩ የፀጥታ አባላቶችን ጨምሮ አጠቃላይ 15 ናቸው።
ከ15 ተከሳሾች መካከል ከ1ኛ እስከ 13ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ቀርበው ጉዳያቸውን በችሎት ተከታትለዋል።
እነዚህ ተከሳሾች በጋምቤላ ከተማ በሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም የሸኔ ሽብር ቡድን እና የጋምቤላ ነጻ አውጪ ፓርቲ (ጋነግ) በጋራ በመሆን በከተማዋ ቀበሌ 03 በኩል በፌደራል ፖሊስ ካምፕ እና በክልሉ ልዩ ኃይል እንዲሁም በሌሎች ፀጥታ አካላት ላይ የከፈቱትን ድንገተኛ ተኩስ ተከትሎ በወቅቱ በፀጥታ ኃይሎች የሽብር ቡድኑ ወደ መጣበት እንዲመለስ ከተደረገ በኃላ ማንነታቸው የተለዩ 35 ሰዎች እና ማንነታቸው ያልተለዩ ሌሎችም ንፁሃን ዜጎችን መረጃ ሰጥታችኋል በሚል ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው እንዲያልፍ ትዕዛዝ በመስጠትና በግድያው የተሳተፉ አሉ ተብለው ተጠርጥረው በዓቃቤ ህግ ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል።
ቀርቦባቸው በነበረው ክስ ላይ በጦርነት ጊዜ ንፁሃን ሰዎችን ለመጠበቅ ሲባል የወጣውን የጄኔቫ ቃል ስምምነት የፕሮቶኮል ድንጋጌን በመተላለፍ እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1 ሀ1/ለ፣ አንቀጽ 35 እና አንቀጽ 270/ሀ ስር የተደነገጉ ድንጋጌዎች መተላለፍ የሚል ነው።
ተከሳሾቹ በዚህ መልኩ የተመሰረተባቸው ክስ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት እንደፈጸሙ ጠቅሰው፤ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ÷ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ ምስክሮች ቀርበው ይሰሙልኝ በማለት አጠቃላይ 37 ምስክሮች እንዳሉት ገልጾ የምስክር ቃል እንዲሰማለት ጠይቆ ነበር።
በፍርድ ቤቱም ዓቃቤ ህግ ካስመዘገባቸው ምስክሮች መካከል አንድ ምስክርን በ10 ተከሳሾች ላይ የሰጠውን የምስክር ቃልና ሌሎች ሁለት የግል ተበዳይ ነን በማለት አስመዝግበው የሰጡት ምስክርነት ቃል አዳምጧል።
የችሎቱ ዳኞች በተለያዩ በሌላ የምድብ ችሎቶች እንዲዘዋወሩ መደረጋቸውን ተከትሎ በሌሎች በሚተኩ ዳኞች በኩል ቀሪ ምስክሮች ቃል የመስማት ሂደቱ በቀጣይ ቀናቶች ይቀጥላል ተብሏል።
በታሪክ አዱኛ