ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንደምትሰራ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ የትብብር መስክ ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት እንደምትሰራ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አወር ገለጹ።
የጀርመን ብሔራዊ የአንድነት ቀን አዲስ አበባ በሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ ዛሬ ተከብሯል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላት፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አወር በመርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያና ጀርመን ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው።
ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሰራም ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በበኩላቸው÷ ጀርመን ለኢትዮጵያ በሁለትዮሽ የትብብር ማዕቀፍ ከምታደርገው የልማት የፋይናንስ ድጋፍ በተጨማሪ በባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በኩል የምታበረክተው ድጋፍ ጠንካራ መሆኑንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተለያዩ የትበብር መስኮች ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያና የጀርመን የሁለትዮሽ ግንኙነት በፈረንጆቹ 1905 መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።