በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ጉብኝት መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
ጉብኝቱ በምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ ኢሉ አባቦራ፣ ምዕራብ ሐርርጌ፣ ባሌ፣ ቦረና እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ነው የተካሄደው፡፡
በጉብኝት መርሐ ግብሩ ባለሃብቶች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡
የጉብኝት ተሳታፊዎች በዞኖቹ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወኑ የሚገኙ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
በዚህም የመንገድ ፕሮጀክቶች፣ የግብርና ሥራዎች፣ የዶሮ፣ የወትተ፣ የከብት ማድለብ እና የንብ ማነብ ሥራዎች እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶች መጎብኘታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የጉብኝቱ ተሳታፊዎች÷ የተሰሩ የልማት ሥራዎች አበረታች እና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
መሰል ሥራዎች በቀጣይ ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡