Fana: At a Speed of Life!

ኡስታዝ አቡበከር የተባለ ግለሰብን በማገት መኪናውን ሊነጥቁ ነበር ተብለው የተጠረጠሩ ፖሊስችን ጨምሮ 7 ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን የተባለ ግለሰብን በማገት ሊብሬውን በመቀየር መኪናውን ሊነጥቁ ነበር ተብለው የተጠረጠሩ ፖሊስችን ጨምሮ 7 ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተ።

ክሱ ከተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል የአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሰራተኞችና ሁለት የፖሊስ አባላት ይገኙበታል።

ተጠርጣሪዎቹ በፌደራል ፖሊስ እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ክትትል በቁጥጥር ስር ውለው በሙስና ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ መሪነት በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ የምርመራ ማጣሪያ ሲደረግባቸው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

የምርመራ መዝገቡ ከተጠናቀቀ በኋላ ዐቃቤ ህግ በጊዜ ቀጠሮ ችሎት በተፈቀደለት የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ መሰረት በዛሬው ዕለት በ7 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መስርቷል።

ክሱ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች 1ኛ ተከሳሽ የሁለተኛ ተከሳሽ ወኪል የሆነው ፍፁም ተክሉ አፅብሀ፣ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ የኡስታዝ አቡበከር ሁሴንን ተሽከርካሪ በስሙ አዙሯል የተባለው አበራ ነጋሳ ሆርዶፋ፣ በአዲስ አበባ አሸከርካሪ ተሸከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አዲስ ከተማ ቅ/ጽ/ቤት ውስጥ የተሽከርካሪ አገልግሎት ባለሙያ ናቸው የተባሉት አብዮት አበራ፣ ልየው አሰፋ አንዱዓለም፣ አለሙ ኦልጅራ እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የንፋስ ስልክ ፖሊስ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ቡድን ኃላፊ ዋና ሳጅን መኳንንት ተመስገን እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኢንተለጀንስ ቡድን አባል የሆነው ዋና ሳጅን ገመቹ ብርሃኑ እንደሆኑ ተመላክቷል።

ከነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዳኞች በአዲስ የችሎት ድልድል ሂደት ላይ በመሆናቸው ምክንያት መዝገቡ ለፊታችን ሰኞ ተቀጥሯል።

የተጠርጣሪዎች የወንጀል ተሳትፎና ዝርዝር ክሱን የችሎቱን ስነስርዓት በጠበቀ መልኩ የፊታችን ሰኞ የምናቀርብ ይሆናል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.