ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን በማጠናከር በወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተስማሙ።
የደቡብ አፍሪካ መከላከያ ሰራዊት ትምህርትና ልማት ዳይሬክተር ከኢፌዴሪ መከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ሀላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮነን ጋር በወታደራዊ ትምህርትና ሥልጠና ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
ሀገራቱ ሠራዊታቸውን ለማዘመን በሚያደርጉት ጥረት ልምድና ተሞክሯቸውን እንዲለዋወጡ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ስምምነት መደረጉን ሌተናል ጀኔራል ይመር መኮንን ገልፀዋል።
የደቡብ አፍሪካ ትምህርትና ልማት ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጀኔራል ዞዲ ሰዋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካ ነፃነት ያበረከተችው አስተዋፅኦ የጎላ እንደነበረ አስታውሰዋል ።
ለዘመናዊ ሰራዊት ግንባታ በጋራ ለመስራት የደረሱበት ስምምነት ለሁለቱም ሀገራት ሰራዊት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
በተለይም ደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልእኮ ስኬቶቿ እና ከአየር ሀይሏ ዘመናዊነት ልምድና ተሞክሮ መውሰድ እንደምትፈልግ ብርጋዲየር ጀኔራል ዞዲ ሰዋ ገልፀዋል።
በዚህ የስምምነት መድረክ ለጀኔራል መኮንኗ ስለ ኢትዮጵያ ዋር ኮሌጅ እና የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ገለፃ ተደርጎላቸዋል።
ብርጋዲየር ጀኔራል ዞዲ ሰዋ ደቡብ አፍሪካ ለኮሌጆቹ በቁሳቁስና በካሪኩለም ቀረፃ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡