Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ህብረት የጋዛ የቦምብ ጥቃት እንዲቆም ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ሲባል የቦምብ ጥቃት እንዲቆም ጠይቋል።
ትናንት በብራስልስ የተጠናቀቀው የሁለት ቀናት የአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በእስራኤል እና ሃማስ እንዲሁም በዩክሬን እና በሩሲያ ግጭት ላይ ተወያይተዋል።
የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሼል በጋዛ ያለው ግጭት መባባስ ለአካባቢው እና ለዓለም እጅግ አደገኛ መሆኑን እና ይህን ለማስወገድ የአውሮፓ ህብረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአውሮፓ ምክር ቤት ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግጋት ጋር በተጣጣመ መልኩ የዜጎችን ጥበቃ ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት በቅርቡ ዓለም አቀፍ የሰላም ጉባኤ እንዲካሄድ ድጋፍ እንደሚያደርግም መሪዎቹ ተናግረዋል።
ጦርነቱ ከጀመረ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሰብዓዊ ድጋፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ቢገቡም አቅርቦቱ በቂ እንዳልሆነ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባለሥልጣን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸው ተጠቅሷል።
የሩሲያ እና የዩክሬንን ግጭት በተመለከተ የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ለዩክሬን የሚያደርጉትን ወታደራዊ ድጋፍ በአውሮፓ የሰላም ተቋም እና በአውሮፓ ህብረት ወታደራዊ እርዳታ ተልዕኮ እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ይሁን እንጂ ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ ለዩክሬን የሚደረገውን አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ያካተተውን የሕብረቱን የ2024 ረቂቅ በጀት ለማጽደቅ ፈቃደኞች አለመሆናቸውን ሺንዋ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.