በግብርና፣ ኢንዱሥትሪና ምኅንድስና ዘርፍ ለተሠማሩ የልማት ድርጅቶች ድጋፍ ይደረጋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርና፣ በኢንዱሥትሪ እና ምኅንድስና ዘርፍ ተሠማርተው ሃብት ለሚያመነጩ የልማት ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የአማራ ክልል አስታወቀ፡፡
የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2016 የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ግምገማ አካሂደዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በውይይቱ ላይ ተገኝተው የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
የልማት ድርጅቶቹ የልማት ክፍተትን በመሙላት የክልሉ የካፒታል እና የቴክኖሎጂ ዓቅም እንዲሆኑ ታስቦ መቋቋማቸውንም አስገንዝበዋል፡፡
አንዳንድ የልማት ድርጅቶች አነስተኛ ውጤት የሚታይባቸውና እየተደገፉ የሚሠሩ በመሆናቸው አዋጪ አይደለም ያሉት አቶ አረጋ÷ ድርጅቶቹ አትራፊ ሆነው ለክልሉ ተጨማሪ አቅም ከመሆን ይልቅ ኪሳራ ውስጥ ገብተው የራሳቸውን ጥሪት ጭምር እያሟጠጡ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ከአቅም በላይ ለሆኑ ችግሮች ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰው÷ የድርጅቶቹ አመራሮች እና የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በጥብቅ ክትትል የሚመራ የሥራ ባሕል መገንባት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ድርጅቶቹ ስኬታቸውን ከዕቅድ ክንውን ይልቅ በጠንካራ ተወዳዳሪነት መለካት እንዳለባቸውም አስረድተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር መሬት፣ የውጪ ምንዛሪ እና የሲሚንቶ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ይሠራል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
የትኩረት መስክ የሆኑ ተቋማትን ለይቶ ማጠናከር እንደሚገባ አመላክተው÷ በግብርና፣ ኢንዱሥትሪ እና ምኅንድስና ዘርፍ ተሠማርተው ሃብት የሚያመነጩ የልማት ድርጅቶችን እንደግፋለን ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!